Fana: At a Speed of Life!

ኢራን ታጣቂ ቡድኖች ላይ የአየር ጥቃት ፈፀመች

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን በፓኪስታን ግዛት የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ የአየር ጥቃት መፈፀሟ ተገለፀ፡፡

ጥቃቱ በእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት እየታመስ የሚገኘውን የመከካለኛው ምስራቅ ቀጠና የበለጠ ውጥረት ውስጥ ለመግባቱ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥቃቱን “ህገ ወጥ” ሲል የገለፀው ሲሆን በጥቃቱ ሁለት ህፃናት መሞታቸውን እና ተጨማሪ ሶስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ በኢስላማባድ የሚገኘውን የቴህራን ከፍተኛ ዲፕሎማት የፓኪስታንን የአየር ክልል በመጣስ ስለተፈፀመው የአየር ጥቃት ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠርቷል ነው የተባለው፡፡

ፓኪስታን ስለ ጥቃቱ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ብትቆጠብም፣ ኢራን የአየር ጥቃት የፈፀመችው ሁለቱ ሀገሮች በሚጋሩት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ድንበር ላይ በምትገኘው ባሎቺስታን ግዛት ላይ መሆኑ ተነግሯል።

ኢራን በበኩሏ ጥቃቱ ለደረሰባት የ80 ሰዎችን ህይዎት የቀጠፈ የሽብር ጥቃት ምላሽ አካል መሆኑን እና የታጣቂ ቡድኖች የጦር ሰፈር ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልፃለች፡፡

ኢራን እና ፓኪስታን በደቡብ ምዕራብ ፓኪስታን የሚገኙ የባሎቺ ተገንጣዮችን እና በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ለረጅም ጊዜ በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸው ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ኢራን የፓኪስታንን የአየር ክልል በመጣስ የፈፀመችው ጥቃት በሁለቱ ሀገራት መካካል መቃቃርን ሊፈጥር ይችላል መባሉን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.