ኤችፒሲ ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ መዋዕለ ንዋዩን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ኤችፒሲ” የተሰኘ የጀርመን ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በዳታ ሴንተር ግንባታ መዋዕለ ንዋዩን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጁነዲን ኩባንያው ባቀረበው ዝርዝር የኢንቨስትመንት ፍላጎት ላይ ከኩባንያው የሥራ ሀላፊ ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
አቶ ዘመን ጁነዲን በወቅቱ÷ ኢትዮጵያ ለዘመናዊ መረጃ አያያዝና የመረጃ ማዕከላት ግንባታ እድገት ለማምጣት እየሰራች መሆኑን በመግለጽ፤ ኮርፖሬሽኑ ለኢንቨስትመንቱ መሳካት እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የኩባንያው የሥራ ሀላፊ በበኩላቸው÷ የኢንቨስትመንት ሀሳባቸውን በዝርዝር አቅርበው በቀጣይም ለኢንቨስትመንቱ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ኢንቨስትመንት ስራዎችን ማከናወን እንደሚጀምሩ አሳውቀዋል።
መቀመጫነቱን አሜሪካን ያደረገውና ባለቤትነቱ የጀርመን የሆነው ኩባንያ ለስራው የሚያግዙ ዳታ ማዕከሎችን በማምጣትና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በመገጣጠም ስራዎችን በመከወን የስራ እድል ፈጠራና የቴክኖሎጂ እንዲሁም የእውቀት ሽግግር ላይ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡
ለዚሁ ተግባር የሚሆን የለማ መሬት ተረክቦ የመስራት ፍላጎት እንዳለው መገለጹን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡