የኢትዮጵያን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት የሚከላከሉ ትጥቆችን መታጠቃችን ይቀጥላል – ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ሊከላከሉ የሚችሉ ዘመናዊ የውጊያ ትጥቆችን መታጠቃችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ፡፡
የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዘመናዊ የሆነውን የመጀመሪያ ዙር የsu-30 ተዋጊ ጀቶችንና የስትራቴጂክ ሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ታጥቋል ተብሏል።
በዚሁ ርክክብ ላይ የተገኙት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ÷ በዓለማችን ላይ ተመራጭ የሆኑትን የsu-30 እና የስትራቴጂክ ሰው አልባ አውሮፕላን ባለቤት መሆናችን በሀገራችን ላይ ሊቃጡ የሚሞከሩ ጥቃቶችን ለማክሸፍ ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የ5ኛ ትውልድ አካል የሆኑት ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖችና የስትራቴጂክ ሰው አልባ አውሮፕላኖች አየር ሀይሉን የማዘመን አንዱ አካል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር ሀይል በአፍሪካ በውጊያ አቅሙ፣ በጀግንነቱና በትጥቁ የነበረውን ዝና ዘመኑ በሚጠይቀው መልኩ ለማዘመን እየተሰሩት ያሉት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ዘመን ተሻጋሪ የአየር ሀይል የመገንባት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው÷ አየር ሀይሉ በሰለጠነ የሰው ሀይል፣ በትጥቅና በውጊያ መሰረተ ልማት መጠናከሩን ጠቁመዋል።
ተቋሙ የተረከባቸው ዘመናዊ የጦር ጀቶች በተመሳሳይ ጊዜ በአየርና በምድር ላይ ያለ የጠላት ታርጌትን ማውደም የሚችል መሆኑን በመግለጽ ዘመናዊ የሰው አልባ አውሮፕላኖችም የጠላትን ዒላማ የማይስቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።