Fana: At a Speed of Life!

 በቀይ ባሕር በሚያልፉ መርከቦች ላይ የሚሠነዘረው ጥቃት የዓለም የንግድ ሥርዓትን አስተጓጉሏል- ሪፖርት

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀይ ባሕር በሚተላለፉ የዕቃ ጫኝ መርኮቦች ላይ የተፈፀመው ተደጋጋሚ ጥቃት የዓለም የንግድ ሥርዓትን ማስተጓጎሉን ሪፖርት አመላከተ፡፡

የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር በሚጓጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ የዓለም የንግድ ልውውጥ በአንድ ወር 1 ነጥብ 3 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የጀርመኑ የኢኮኖሚ ቲንክ ታንክ ግሩፕ ኪየል ኢንስትቲዩት አመላክቷል፡፡

በቀይ ባሕር የሚተላለፉ የኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች ቁጥርም 70 በመቶ ቀንሷል ያለው ሪፖርቱ÷ ለአብነትም በሕዳር ወር በቀን ከ500 ሺህ በላይ መርከቦች ሲጓጓዙ እንደነበር አስታውሶ አሁን ወደ 200 ሺህ ዝቅ ማለቱን አብራርቷል፡፡

ዕቃዎችን ከአፍሪካ ወደ እስያ እና አውሮፓ ለማጓጓዝ እስከ 20 ቀን እንደሚፈጅ እና ይህም የዓለም የንግድ ልውውጥን ማስተጓጎሉ ተጠቅሷል፡፡

በቀይ ባሕር ላይ በተስተዋለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት የወጪ እና ገቢ ንግዳቸው በ2 በመቶ እና በ3 ነጥብ 1 በመቶ ቀንሷል ነው የተባለው፡፡

በተመሳሳይ የአሜሪካ የወጪ ንግድ በ1 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም የገቢ ንግዷ በ1 በመቶ መቀኑሱን ጠቅሶ አርቲ ዘግቧል፡፡

የሁቲ አማፂያን ባለፈው ወር በቀይ ባሕር ሲጓዙ በነበሩ ንብረትነታቸው የአሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት በሆኑ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡

በአንጻሩ የቀይ ባሕርን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚል አሜሪካ እና ብሪታኒያ በየመን የሁቲ አማፂያን ይዞታዎች ናቸው ባሏቸው 16 ዒላማዎች ላይ ድብደባ መፈፀማቸው ይታወቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.