የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 41ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር መጠናቀቁን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በ6 ኪሎ ሜትር የወጣት ሴቶች ሩጫ አትሌት የኔዋ ንብረት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስታሸንፍ አሳየች አድነው በተመሳሳይ ከንግድ ባንክ 2ኛ እንዲሁም ሽቶ ጉሚ ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
እንዲሁም በ8ኪሎ ሜትር የወጣት ወንዶች ውድድር አትሌት አቤል በቀለ ከሸገር ከተማ ቀዳሚ ሆኗል፡፡
በዚሁ የውድድር መርሐ-ግብር የኢትዮ ኤሌክትሪኮቹ አትሌት ሳሙኤል ፍሬው 2ኛ፣ ጀንበሩ ሲሳይ ደግሞ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቃቸውን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ መርሐ-ግብር የ10ኪሎ ሜትር የአዋቂ ሴቶች የሩጫ ውድድርን አትሌት ግርማዊት ገ/እግዚአብሔር ከጉና ንግድ አሸንፋለች፡፡
በዚሁ ውድድር አትሌት ታደለች በቀለ ከኦሮሚያ ክልል 2ኛ እና መሰረት ጎላ ከኢትዮ አሌክትሪክ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የ10ኪሎ ሜትር የአዋቂ ወንዶች ሩጫን ደግሞ አትሌት ቦኪ ድሪባ ከሸገር ከተማ 1ኛ በመውጣት ሲያጠናቅቅ÷ የኢትዮ ኤሌክትሪኮቹ ታደሠ ወርቁ እና በሪሁ አረጋዊ 2ኛ እና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ጨርሰዋል፡፡
በቡድን ውድድር ደግሞ በ6 ኪሎ ሜትር የወጣት ሴቶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ26 ነጥብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በተመሳሳይ በ8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች በ27 ነጥብ፣ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች በ27 ነጥብ እና በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች 22 ነጥብ በመሰብሰብ ኢትዮ ኤልክትሪክ ዋንጫ ተሸልሟል፡፡