ኬፕ ቨርዴ ወባን በማጥፋት 4ኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ሆነች
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኬፕ ቨርዴ ወባን በማጥፋት ከአፍሪካ አራተኛዋ ከዓለም ደግሞ 44ኛዋ ሀገር መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡
አልጄሪያ፣ ሞሮኮ እና ሞሪሺየስ በፈረንጆቹ 2019፣ 2010 እና 1973 እንደቅደም ተከተላቸው ከወባ በሽታ ነፃ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በፈረንጆቹ 2022 በአፍሪካ በወባ በሽታ ከተያዙ ታማሚዎች መካከል 95 በመቶ ያህሉ ሕይወታቸው ማለፉን ድርጅቱ አስታውሷል፡፡
ኬፕ ቨርዴም በ 10 ደሴቶች ላይ ከባድ የወባ ወረርሽኝ አጋጥሟት እንደነበር አስታውሶ ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ከፈረንጆቹ 1980ቹ ጀምሮ በሁለት ደሴቶቿ ማለትም ሳንቲያጎ እና ቦአ ቪስታ ብቻ ወባ ስርጭቱ ተወስኖ የቆየ ቢሆንም በእነዚህ አካባቢዎች ከ2017 ጀምሮ ምንም ታማሚ አለመመዝገቡ ተነግሯል።
የዓለም ጤና ድርጅትም ሀገሪቱ የወባ በሽታን ለማጥፋት ረዥም ርቀት መጓዟን ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ነፃ ሕክምና በመስጠት፣ ወደ ሀገሪቱ ለሚገቡ ሁሉም ሰዎች ምርመራ በማድረግ፣ ዓመቱን ሙሉ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ተከታትሎ በማፅዳት ሰፊ ሥራ መሥራቷንም በመረጃው አመላክቷል፡፡
እነዚህ ስልቶች በቀጣይም እንደ ዴንጊ ትኩሳት ያሉ ሌሎች በወባ ትንኝ የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምም የኬፕ ቨርዴ መንግሥት እና ሕዝብ የወባ በሽታን ለማጥፋት ላሳዩት ቁርጠኝነት አመሥግነዋል፡፡
የኬፕ ቨርዴ ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታን ለመከላከል እና ከወባ ነፃ ዓለምን ለመፍጠር የሚደረገውን ትግል ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ተስፋ ሰጪ ተሞክሮ መሆኑንም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡ FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!