ትምህርት ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያ ጋር በትምህርት ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማማ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያ ጊዮንግሳንግቡክ-ዶ ትምህርት ቢሮ ጋር በትምህርት መረጃ ልውውጥና ትብብር ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የትብብር መግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ እና የጊዮንግሳንግቡክ-ዶ ቢሮ የትምህርት ዘርፍ አስተዳዳሪ ሊም ጆንግ-ሲክ ተፈራርመዋል፡፡
የትብብር ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ከ2016 እስከ 2017 ዓ.ም የሚደረገውን የትምህርት መረጃ ልውውጥና ትብብርን የተመለከተ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ወዳጅነት ከማጠናከሩ ባሻገር በዲጂታል የትምህርት ስትራቴጂና የማስፈጸሚያ ዕቅድ አተገባበር እንዲዳብር ያስችላል መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በስምምነቱ የአይሲቲ መሳሪያዎችን ማቅረብና ለተመረጡ መምህራን ከትምህርታዊ መረጃ አሰጣጥ ጋር የተያያዘ ስልጠና መስጠት የደቡብ ኮሪያ መንግስትን እንደሚመለከት ተጠቅሷል፡፡
የስልጠና ተሳታፊዎችን መምረጥ ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴርን እንደሚመለከት በሰነዱ መካተቱ ተጠቁሟል፡፡