በአማራ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ድጋፍ መቀጠሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖች በመንግስት፣ በልማት ድርጅቶችና ባለሃብቶች የሚደረገው ድጋፍ እንደቀጠለ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስትሪንግ ኮሚቴ ድርቁ ያስከተለውን ጉዳትና በሃብት ማሰባሰብ ዙሪያ ዛሬ ምክክር አካሄዷል።
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል እንዳመለከቱት፤ በክልሉ 43 ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለምግብ እህል እጥረት ተጋልጧል።
ችግሩን ለማቃለል የክልሉ መንግስት 430 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቅሰው፤ የፌዴራል መንግስትም በመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለሚበልጡ ተጠቃሚዎች የምግብ እህል እንዲደርስና እንዲመቻች ማድረጉን ገልጸዋል።
ባንኮች፣ የልማት ድርጅቶችና ባለሃብቶችም የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶችም የችግሩን ስፋት በመረዳት ምላሽ መስጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም ሆነ በሌሎች የክልሉ ስፍራዎች የመስኖ ልማቱን አጠናክሮ በማስቀጠል የምግብ እህልና የእንስሳት መኖ አቅርቦት እንዲኖር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ስትሪንግ ኮሚቴው መመከሩን አስረድተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊና የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ግብረ ሃይል ሰብሳቢ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ እርዳታን በፍጥነት በማድረስ፣ ትክክለኛ ተረጅዎችን በመለየትና ተጠቃሚ በማድረግ፣ እርዳታው ወደ ማዕከል ከገባ በኋላ በፍጥነት በማሰራጨት በኩል ውስንነቶች መስተዋላቸውን ጠቅሰዋል።
የተካሄደው ውይይትም እነዚህና ሌሎች ችግሮችን ለይቶ በቀጣይ ተስተካክለው መንግስት፣ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችና ባለሃብቱ የሚያቀርበው እርዳታ በፍትሃዊነት ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ለማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን ድርቁን አስመልክቶ እየተደረገ ያለው ምላሽ ተስፋ ሰጭ ነው ያሉት ዶክተር ድረስ፤ በቀጣይ በግብርናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት አርሶ አደሩ የአንድ ዓመት ጥሪት የሚይዝበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመስኖ ልማቱን ለማጠናከር ምርጥ ዘር፣ የውሃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችና ሌሎች ቁሳቁሶች በማቅረብ ላይ በማተኮር እንደሚሰራ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።