ለትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የተላለፈው ጥሪ ቱሪዝምን ከማነቃቃት የተሻገረ ፋይዳ አለው – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ቀደምት ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ መተላለፉ ቱሪዝምን ከማነቃቃት እና ትሥሥርን ከመፍጠር የተሻገረ ፋይዳ እንዳለው ምሁራን ገለጹ፡፡
የጥሪውን ዓላማ ከግብ ለማድረስም ኤምባሲዎችና ቆንስላ ፅህፈት ቤቶች ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎትና ማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲ የቱሪዝም እና ሆቴል አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ካሰኝ ብርሃኑ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከወገናቸው ጋር ከሚፈጥሩት ትሥሥር እንዲሁም ታሪክ ፣ ባሕል እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማወቅ ባሻገር በልማት እና ኢንቨስትመንትም አሻራቸውን እንዲያኖሩ ይረዳል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም መምህር ፣ ተመራማሪና አማካሪ አሰግድ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ በውጭ ያሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ፅህፈት ቤቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቀንቋዎችና በማኅበራዊ የሚዲያ አውታሮች የማስተዋወቅና የማነሳሳት ሚናቸውን በሚገባ መወጣት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የዳያስፖራ አገልግሎት የማኅበረሰብ ልማት ተጠባባቂ ዳሬክተር ነብዩ ሶሎሞንም ÷ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን መረጃ እንዲደርሳቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ከኤምባሲዎች እና ቆንስላ ፅህፈት ቤቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሐ ግብሩ መሰረት በመምጣት መነሻቸውን፣ ታሪካቸውን እና ባሕላቸውን እንዲያውቁ ከወገናቸው ጋርም ጠንካራ ትሥሥር እንዲፈጥሩ አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ በልማቱ ዘርፍ ያሉትን አማራጮች እንዲቃኙም ነው የጠየቁት፡፡
በማርታ ጌታቸው