Fana: At a Speed of Life!

የባለስልጣን ዘመድ እንደሆኑና ሲሚንቶ አስመጪ ነን በማለት በማታለል ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣን ዘመድ እንደሆኑ በማስመሰልና ሲሚንቶ አስመጪ ነን በሚል በማታለል ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉ ተከሳሾች በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ነው።

ተከሳሾቹ የስንቄ ባንክ ፍቼ ቅርጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ እንዳለ ዋቅቶላ እና የትዳር አጋሩ ወ/ሮ ሀዊ ፋጂ ናቸው።

የክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው 1ኛ ተከሳሽ የትዳር አጋሩ የሆነችው 2ኛ ተከሳሽ አንድ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣን እህት እንዲሁም ሌላ ባለስልጣን ደግሞ አጎቷ እንደሆነ ለተለያዩ ግለሰቦች በመንገርና በሀሰት እምነት እንዲጥሉባት አድርጓል በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል።

2ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሲሚንቶ አስመጣለሁ በማለት በተለያዩ ጊዜያት ግለሰቦችን በማታለል በ2015 ዓ.ም ከአንድ የግል ተበዳይ 960 ሺህ ብር ከሌላኛው የግል ተበዳይ ደግሞ 600 ሺህ ብር በባንክ ሂሳቧ ገቢ እንዲደረግላት ማድረጓ ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ገልጿል።

ሁለቱም ተከሳሾች የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በአታላይነት ወንጀል ተከሰዋል።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦባቸዋል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግን መከራከሪያ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ የመከላከያ ማስረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱም የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት መርምሮ ተከሳሾቹን በ7 አመት ከ8 ወራት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.