የቻይናዋ ሀርቢን ከበዓል ሰሞን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከ800 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናዋ ሀርቢን ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በዓል ሰሞን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከ800 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ፡፡
በሰሜን ምሥራቅ ቻይና ሄይሎንግጂያንግ ግዛት የምትገኘዋ ከተማ ይህን ያህል ገቢ የሰበሰበችው በሦስት ቀናት የአዲስ ዓመት በዓል የቱሪዝም ዘርፍ ዝግጅት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ከተማዋን የተጨናነቀ የቱሪስት መናኸሪያ ያደረጋት የክረምት የበረዶ ግግሯ፣ ከበረዶ የተሠሩ ቅርፃ ቅርፆቿ፣ የተለያዩ የክረምት ስፖርታዊ ዝግጅቶች እንዲሁም የመዝናኛ ሥፍራዎቿ መሆናቸውንም ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የነዋሪዎቿ ሞቅ ያለ አቀባበል እና መስተንግዶም እንዲሁ ቀላል ሥፍራ የሚሰጠው አይደለም ነው የተባለው፡፡
የቻይናን የቱሪዝም መዳረሻዎች እና መረጃዎች በበይነ መረብ በማስተዋወቅ የሚታወቀው “ቶንቼን ትራቭል” የከተማዋን መስኅቦች ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ቀላል ሚና አልነበረውም፡፡
በተለይ የከተማዋ ማዕከላዊ ጎዳና በሦስቱ ቀናት 3 ሚሊየን የሚጠጉ ጎብኚዎችን መቀበሉ ነው የተነገረው፡፡
100 ሺህ አይስክሬሞች መሸጣቸውም ነው የተመላከተው፡፡