Fana: At a Speed of Life!

የአብሮነት ሣምንት የማጠቃለያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከታኅሣስ 20 እስከ 25 በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር የነበረው “የአብሮነት ሣምንት” የማጠቃለያ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ለቀናት ሲካሄድ የቆየው መርሐ-ግብር በዛሬው ዕለት ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተሳተፉበት ይጠቃለላል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ÷ የአብሮነትን በተለየ መልኩ ለማሰብ የተፈለገው ብዝኀነታችን የሚያስተሳስረን መገለጫችን መሆኑን ለማጉላትና ድንቅ የሆኑ የአብሮነት ዕሴቶቻችን ለማንሳት ነው ብለዋል።

እንደ ዕድር እና ዕቁብ ያሉ መገለጫዎቻችን እንዲሁም በባዕዳን ወረራ ወቅት የሚታይ አንድነታችን ዘመናት ለተሻገረው የአብሮነት ዕሴታችን አብነት ሊሆን የሚችል እንደሆነም አንስተዋል።

ሀገረ መንግሥትን በማፅናት ሂደት ውስጥ ፈተናዎች ይኖራሉ ያሉት ሚኒስትሩ፥ ብዝኀ ባሕል፣ ቋንቋና ዕምነትን ባከበረ መልኩ ልንጓዝ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው÷ አባቶች የጣሉትን የአብሮነት መሠረት በመተግበር የጋራ ዕሴቶቻችንን ማፅናት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የዘንድሮው የአብሮነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።

መርሐ-ግብሩ በመድረኩ የተገኙትን ጨምሮ ከሀገር ውስጥና ከመላው ዓለም ከ100 ሺህ በላይ ታዳሚዎች ደቦ በተሰኘ ሀገራዊ መተግበሪያ አማካይነት በበይነ መረብ ይሳተፋሉ ተብሏል።

አብሮነት ላይ ያተኮሩ ሁለት ጥናታዊ ፅሑፎችም ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል ተብሏል፡፡

በወንድሙ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.