በኢራን በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ 73 ሰዎች ሞቱ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢራን የጄኔራል ቃሲም ሱለይማኒን 4ኛ የሙት አመት እያከበሩ በነበሩ ሰዎች ላይ በደረሰ ሁለት የቦንብ ፍንዳታ 73 ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል፡፡
ፍንዳታው በደቡባዊ ኢራን በምትገኘው ካርማን ከተማ ሳሄብ አል-ዛማን በተባለው መስጊድ አቅራቢያ የተፈፀመ ሲሆን በፍንዳታው ከ171 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም ተሰምቷል፡፡
የካርማን ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ የቦንብ ፍንዳታው የሽብር ጥቃት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአሜሪካ እንደተገደለ በሚነገረው የኢራን የፀረ ሽብር ዘመቻ አዛዥ ቃሲም ሱሊይማኒ 4ኛ የሙት ዓመት ለማስታወስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመቃብሩ ስፍራ በመገኘት ጄኔራሉን ሲያስታውሱ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ከአያቶላህ አሊ ሃሚኒ በመቀጠል በኢራን ወታደራዊ ሀይል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጄኔራል ቃሲም ሱሊይማኒ በ2020 በኢራቅ ባግዳድ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡