Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በዩክሬን በርካታ ከተሞች ላይ በአንድ ቀን ውስጥ ሰፊ ጥቃት ማካሄዷ ተገልጿል።
 
ዛሬ ንጋት ላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች በኪየቭ፣ ኦዴሳ፣ ዲኒፕሮፔትሮቭስክ፣ ካርኪቭ እና ሊቪቭ ከተሞች ላይ ድብደባ ማከሄዳቸውን ተከትሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአየር ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ተመላክቷል።
 
ጥቃቱ የተፈጸመው ዩክሬን በክሬሚያ ወደብ ፌዮዶሲያ ውስጥ የሩሲያን የጦር መርከብ ካወደመች ከቀናት በኋላ መሆኑ ተጠቁሟል።
 
ከዚህ በተጨማሪም ጥቃቱ የተሰነዘረው የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የአየር መከላከያ ተተኳሾችን ጨምሮ 250 ሚሊየን ዶላር ወታደራዊ የድጋፍ ማዕቀፍ መፅደቁን ተከትሎ ለአሜሪካ ምስጋና ካቀረቡ ከአንድ ቀን በኋላ እንደሆነም ቢቢሲ ዘግቧል።
 
ከባድ እንደሆነ በተገለጸው በዚህ ጥቃት በመላ ሀገሪቱ በርካታ ሰዎች ሲቆስሉ ቢያንስ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ የተገለጸ ሲሁን፤ በመላ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስ እንዳልቀረ ተነግሯል።
 
የኪየቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ በቴሌግራም ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት የአየር መከላከያ ጥቃቱን ለመመከት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ያም ሆኖ ግን ዜጎች በመጠለያ ውስጥ እንዲቆዩ አሳስበዋል።
 
የካርኪቭ ከንቲባ ኢጎር ቴሬክሆቭ በበኩላቸው በከተማዋ ላይ በተደረጉ ተከታታይ ጥቃቶች የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ቆስለዋል ብለዋል።
 
በሀገሪቱ ምዕራብ የምትገኘው የሊቪቭ ከተማ ከንቲባ አንድሪ ሳዶቪ÷ በከተማዋ ላይ ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች መፈፀማቸውን ገልፀዋል።
 
የፕሬዚዳንቱ ረዳት አንድሪ ይርማክ “የአየር መከላከያችንን ለማጠናከር የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው፣ ነገር ግን ዓለም ይህን ሽብር ለማስቆም ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልገን ማጤን አለበት” ሲሉ በቴሌግራም ገጻቸው ማስፈራቸው ተዘግቧል፡፡
 
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.