ኒው ዴልሂ ከተማ እንቅስቃሴን በሚያውክ ከባድ ጭጋግ መዋጧ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ ዋና ከተማ ኒው ዴልሂ እና በሰሜን የህንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ቅዝቃዜ እና ጥቅጥቅ ያለ ጭጋግ የጉዞ እንቅስቃሴን እያደናቀፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም የተነሳ በከተማዋ ከ100 በላይ በረራዎች እና 25 የባቡር ጉዞዎች እንዲዘገዩ መደረጋቸውም ተመላክቷል።
ከተማዋ ከወቅቱ ጭጋጋማ ቀናት አንዱን እያስተናገደች ሲሆን÷ በዛሬው ዕለት የእይታ ሁኔታውም ከ50 ሜትር ርቀት በታች መውረዱም ነው የተገለጸው።
ጭጋጉ የጉዞ እንቅስቃሴ ላይ ባሳረፈው ተጽዕኖ በዝግታ ለመጓዝ ከማስገደድ ባለፈ በአንዳንድ አካባቢዎችም አደጋ ጭምር ማስከተሉ ተነግሯል፡፡
ዛሬ ማለዳ የኡታር ፕራዴሽ ግዛት በጥቅጥቅ ጭጋግ መሸፈኑን ተከትሎ በፍጥነት መንገድ ላይ በርካታ ተሽከርካሪዎች እንደተገጫጩ ተሰምቷል።
ከቦታው የተነሱ ፎቶዎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችም የተሰባበሩ የመኪና ክፍሎች ጭጋጋማ በሆነው መንገድ ላይ ወድቀው አሳይተዋል።
በአደጋው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም በርካታ ሰዎች ግን መቁሰላቸው ተገልጿል።
የተለያዩ የሰሜን እና የመካከለኛው ህንድ አካባቢዎች ቀዝቃዛ ሞገዶች ስለሚያጋጥማቸው በየዓመቱ በዚህ ወቅት ጥቅጥቅ ያለ ጭጋግ በአካባቢው የተለመደ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ሰሜን ክፍሎች÷ በፑንጃብ፣ ሃሪያና፣ ኡታር ፕራዴሽ፣ ማድያ ፕራዴሽ፣ ራጃስታን እና ህንድ በምታስተዳድረው ካሽሚር ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ እንደቀጠለ መሆኑ ተጠቁሟል።
ጭጋጋማው ሁኔታ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት እንደሚቀጥል ያስጠነቀቀው የሕንድ የአየር ሁኔታ ቢሮ፤ አሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ ለተሻሻለ እይታ የጭጋግ መብራቶችን በመጠቀም በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩ ማሳሰቡን ቢቢሲ ዘግቧል።
ድንገተኛ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ሰዎች ወደ ውጭ እንዳይወጡ እና ከቤት ውጭ በሚሆኑበት ጊዜ ፊታቸውን በሚገባ እንዲሸፍኑም ጠይቋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!