የፈረንጆቹ 2024 ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚመዘገብበት ዓመት እንደሚሆን ሳይንቲስቶች አስጠነቀቁ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈረንጆቹ 2024 ሌላኛው ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚመዘገብበት ዓመት ሊሆን እንደሚችል ሳይንቲስቶች አስጠንቅቀዋል፡፡
በሙቀት መጠን እየጨመረ መምጣት እና በኤልኒኖ የአየር ሁኔታ የተነሳ የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን ከወትሮው ከፍ እያለ እንደሚሄድም ገልጸዋል፡፡
ከዚህም አኳያ የፈረንጆቹ 2024 ሌላ ክብረ ወሰን የሚመዘገብበት ሞቃታማ ዓመት እንደሚሆን ነው ያመላከቱት፡፡
በፈረንጆቹ 2023 በዱባይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ÷ ሀገራት ታዳሽ ያልሆነ ኃይልን ከመጠቀም እንዲወጡ የሚጠይቅ ስምምነት ቢደረስም፣ በሂደት ሙሉ ለሙሉ መውጣት ላይ ግን ስምምነት ሳይደረስ መቅረቱንም አንስተዋል።
ታዳሽ ያልሆነ ኃይልን በመጠቀም የተነሳ ዓለም በዓመቱ ያልተለመደ በጣም ሞቃታማ የአየር ሁኔታን ለማስተናገድ ተገዳ እንደነበር ሳይንቲስቶቹ አመላክተዋል፡፡
የፈረንጆቹ ሐምሌ ወር በታሪክ በጣም ሞቃታማው ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን÷ ከዚያ ወዲህ ነሐሴ፣ መስከረም፣ ጥቅምት እና ህዳር ወራትም በዓመቱ ክብረ ወሰን የሰበሩ ሞቃታማ ወራት ሆነው ማለፋቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው ሲሉም በአውሮፓ መካከለኛ የአየር ሁኔታ ትንበያ ማዕከል የኮፐርኒከስ የአየር ንብረት ለውጥ አገልግሎት ዳይሬክተር ካርሎ ቦንቴምፖ ለአናዶሉ ተናግረዋል።
የዓለም ከፍተኛ የሙቀት መጠን ኤልኒኖን ተከትሎ እንደሚለካ የገለፁት ዳይሬክተሩ÷ ምንም እንኳን በፀደይ ወቅት እንደሚቀንስ ቢጠበቅም ከከፍተኛው የኤልኒኖ የአየር ሁኔታ የተነሳ 2024 ሌላኛው በከፍተኛ ሙቀት ማዕበል የሚመታ ዓመት እንደሚሆን ተናግረዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!