የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሰኔ 10 ወደ ውድድር ሊመለስ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሰኔ 10 ቀን ወደ ውድድር ሊመለስ መሆኑ በዛሬው እለት ተገልጿል።
ፕሪምየር ሊጉ ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል እንዲሁም አስቶንቪላ ከ ሼፍልድ ዩናይትድ በሚያደርጓቸው ተስተካካይ ጨዋታዎች እንደሚጀምርም ታውቋል።
ከዚያ በመቀጠል ከሰኔ 12 እስከ 14 ደግሞ ሙሉ 10 ጨዋታዎች እንደሚካሄዱም የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በፕሪምየር ሊጉ ዳግም መጀመር ዙሪያ ክለቦች በውይይት ላይ ናቸው የተባለ ቢሆንም፤ ሁሉም ክለቦች ግን በመርህ ደረጃ ከመስማማት ላይ መድረሳቸውም ነው የተነገረው።
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ 92 ጨዋታዎች የሚቀሩት ሲሆን፥ ሁሉም የሊጉ ውድድሮች በከፍተኛ ጥንቃቄ ደጋፊ ባልተገኘበት በባዶ ስታዲያም እንደሚካሄዱም ተነግሯል።
በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለሚሳተፉ 2 ሺህ 752 ተጫዋቾችና የስታፍ አባላት በተደረገ ምርመራም እስካሁን 12 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱም ተገልጿል።
በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለሚሳተፉ ሁሉም ተጫዋቾች እና የስታፍ አባላት በየሁለት ሳምንቱ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ይደረጋል የተባለ ሲሆን፥ ቫይረሱ የተገኘበት ማንኛውም ሰው ራሱን ለ7 ቀናት አግልሎ የመቆየት ግዴታ እንዳለበትም ታውቋል።
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ሊቨርፑል በ82 ነጥብ ሲመራ፣ ማንቸስተር ሲቲ በ57 ነጥብ 2ኛ፣ ሌሰተር ሲቲ በ53 ነጥብ 3ኛ እንዲሁም ቸልሲ በ48 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ምንጭ፦ ቢቢሲ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።