Fana: At a Speed of Life!

የጸጥታው ምክር ቤት በጋዛ እርዳታ እንዲገባ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ አፀደቀ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 12 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በጋዛ እርዳታ እንዲገባ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ለቀናት ሲያራዝመው በቆየው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ በዛሬው እለት ተግባራዊ እንዲደረግ ማጽደቁን ቢቢሲ አስነብቧል።

የውሳኔ ሀሳቡን ብሪታንያን ጨምሮ 13 ሀገራት ያጸደቁት ሲሆን፥ አሜሪካ እና ሩሲያ ደግሞ ድምጸ ተዐቅቦ ማድረጋቸውን ዘገባው አስነብቧል።

በዛሬው እለት የጸደቀው ይህ የውሳኔ ሃሳብ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አማካኝነት የቀረበ ነበር።

በምክር ቤቱ የጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ ወደ ጋዛ እርዳታ እንዲገባ እንጅ አሁን ያለው ጦርነት እንዲቆምና ተኩስ አቁም እንዲደረስ የሚጠይቅ አይደለም ነው የተባለው።

በውሳኔ ሃሳቡ መሰረት ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ሳይስተጓጎል እንዲደርስ በሚደረገው ጥረት ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ ነው የተባለው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እስራዔል የምትፈጽመው ጥቃት ተመድ ለሚያደርገው የእርዳታ ጥረት ‘ችግር’ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም “ አሁንም ቢሆን የጋዛ ነዋሪዎች ፍላጎት እንዲሟላና አስፈሪ ህልማቸው እንዲያበቃ ሰብአዊ ተኩስ አቁም ብቸኛ መፍትሄ ነው” ብለዋል።

ሩሲያ የምክር ቤቱ ውሳኔ አሁንም ቢሆን ለእስራዔል የበለጠ ነጻነት የሚሰጥ ነው በሚል ‘ገደብ’ እንዲበጅለት ጠይቃለች።

ከዚህ ባለፈም ‘የውሳኔ ሀሳቡ ግጭት እንዲቆም የሚያስገድድ አንቀጽ ሊኖረው ይገባል’ በሚል ያቀረበችው ሃሳብ በአሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት አልፀደቀም።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.