Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ91 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለማሰልጠን ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከ91 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለማሰልጠን ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ወላጆች መስፈርቱን የሚያሟሉ ተማሪዎች ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በመሄድ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ግፊት ማድረግ አለባቸው ብሏል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አማረ አለሙ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ÷ በክልሉ 236 የመንግስት እና የግል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ይገኛሉ።

በኮሌጆቹ በትምህርት ሚኒስቴር የመግቢያ ውጤት መሰረት 91 ሺህ 916 ተማሪዎችን ከደረጃ 1 እስከ 5 በመደበኛ ትምህርት ለማስተማር እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል።

ተመዝግበው ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩ እንዳሉ ጠቅሰው ÷ ቀሪ ተማሪዎቹ ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሄደው እንዲመዘገቡና ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ወላጆች አስፈላጊውን ትብብርና ግፊት በማድረግ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

በተመሳሳይ ቢሮው በበጀት ዓመቱ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸው ፥ እስካሁን መፍጠር የተቻለው 110 ሺህ ለሚሆኑት ብቻ እንደሆነም መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በመሆኑም የስራ እድል ፈጠራው በታሰበው ልክ ማከናወን እንዲቻል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.