ሰሜን ኮሪያ ትንኮሳ የሚፈጸምባት ከሆነ ኒውክሌር ከመጠቀም እንደማታመነታ አስጠነቀቀች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ ከጠላቶቿ ትንኮሳ የሚፈጸምባት ከሆነ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከመጠቀም ወደ ኋላ አንደማትል አስታወቀች፡፡
የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሀገሪቱ ጦር ሰሞኑን አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳኤል በስኬት ማስወንጨፉን አወድሰዋል፡፡
ኪም ባላስቲክ ሚሳኤሉን በስኬት ካስወነጨፉ ወታደራዊ አመራሮች ጋር በመገናኘት ላከናወኑት ስራ አመስግነው፤ የተወነጨፈው አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል የፒዮንግያንግን ወታደራዊ የማድረግ አቅም ያሳየ ነው ሲሉ አሞካሽተዋል፡፡
ኪም ጆንግ ኡን ጠላቶች ከዚህ ሊማሩ እና ሊፈሩን ይገባል ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
ጠላቶች በሰሜን ኮሪያ ላይ ትንኮሳ የሚፈጽሙ ከሆነም ሀገራቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከመጠቀም እንደማታመነታ ነው ያስገነዘቡት፡፡
በቀጣይ የሰሜን ኮሪያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሀገሪቱ ጦር ከምንጊዜውም በላይ ወታደራዊ አቅሙን ማዘመን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ያስወነጨፈችው ባለስቲክ ሚሳኤል 15 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የመጓዝ አቅም እንዳለው ተመላክቷል፡፡
ይህም የጃፓንን ሁሉም አካባቢዎች እና የአሜሪካን ዋና ዋና ግዛቶች ማካለል እንደሚያስችል ነው የተገለጸው፡፡
ድርጊቱን ተከትሎም አሜሪካ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በቀጣናው ተጨማሪ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማካሄዳቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡