ደቡብ አፍሪካ ዩክሬንና ሩሲያ የሠላም ድርድር እንዲጀምሩ ጠየቀች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ አፍሪካ ዩክሬን እና ሩሲያ የሠላም ድርድር እንዲጀምሩ ጠይቃለች፡፡
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ከኤስ ኤ ቢ ሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግጭት እንዲያበቃ መሪዎቹ ሠላማዊ ውይይት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ሁለቱን ሀገራት ለማሸማገልም ደቡብ አፍሪካ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ድርድር የሚባለው ሐሳብ ጥቅም እንደሌለው እና ዩክሬን ዕርቀ ሠላሙን ብትፈልግም በሩሲያ ተቀባይነት እንደማያገኝ ባሳለፍነው ማክሰኞ መግለጻቸውን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል፡፡
ይሁን እንጂ ደቡብ አፍሪካ ጥያቄውን ካቀረበች ወዲህ በጉዳዩ ላይ ከሁለቱም ወገን ምላሽ አለመሠጠቱን ነው ሚኒስትሯ ያስታወቁት፡፡
ደቡብ አፍሪካ ከሌሎች ሀገራት ጋር በጥምረት በመሆን በአራት የዩክሬን ሩሲያ “የሠላም ሥብሰባዎች ላይ መሳተፏንም አስታውሰዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት በስብሰባው ላይ ግን አንድም ጊዜ የሩሲያ ተወካዮች ጥሪ ቀርቦላቸው ተገኝተው አያውቁም፡፡
አሁንም ቢሆን ደቡብ አፍሪካ ሁለቱን ሀገራት ለማሸማገል ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡