የቴክሳሷ እመቤት በ90 ዓመታቸው የማስተርስ ዲግሪያቸውን አጠናቀቁ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቴክሳስ የ90 ዓመቷ ሴት የሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) ትምሕርታቸውን አጠናቀው መመረቃቸው ተገለጸ፡፡
የ90 ዓመቷ የዕድሜ ባለፀጋ የሁለተኛ ዲግሪ ትምሕርታቸውን በሰሜን ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በማጠናቀቅ የመጀመሪያዋ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡
ሚኒ ፔይን የተባሉት እኝህ አዛውንት የሁለተኛ ዲግሪ ትምሕርታቸውን ያጠናቀቁት “ኢንተር ዲሲፕሊነሪ ስተዲስ ” የትምሕርት መሥክ መሆኑንም ዩ.ፒ.አይ አስነብቧል፡፡
አዛውንቷ ሴት ከ30 ዓመታት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ በ68 ዓመት ዕድሜያቸው ጡረታ ሲወጡ ትምህርታቸውን ከዳር ለማድረስ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማቅናት መወሰናቸው ተነግሯል፡፡
ፔይን ከሃይስኩል እንደተመረቁ የኮሌጅ ትምሕርታቸውን ለአጭር ጊዜ ሲከታተሉ ቆይተው እስከ ጡረታ ወደ ቆዩበት ከፅሑፍ እና ሕትመት ጋር የተያያዘ ሥራ መግባታቸው ተመልክቷል፡፡
ከጡረታ በኋላ ÷ ቴክሳስ ከሚገኘው የሴቶች ዩኒቨርሲቲ ሦስት የጋዜጠኝነት እና አንድ የንግድ ሥራ ትምሕርት ኮርሶች ወስደው ማጠናቀቃቸውን የዜና ምንጩ አስነብቧል፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪ ትምሕርታቸውን በፈረንጆቹ 2006 ላይ በ`ጀነራል ሣይንስ` የትምሕርት መሥክ ማጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡