ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሻንጋይ ከተማ ከንቲባ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የልዑካን ቡድናቸው ከሻንጋይ ከተማ ከንቲባ ጎንግ ዜንግ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ለ50 አመታት የዘለቀው የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማንኛውም ሁኔታ ፀንቶ የሚቆይ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማደጉ በአዲስአበባ እና በሻንጋይ ከተሞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመስራት ከቀድሞ ይበልጥ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
አያይዘውም የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር በፋይናንስ፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ እና በማምረቻው ዘርፍ ባስመዘገበችው አስደናቂ ልማት ከምትታወቀው ከሻንጋይ ከተማ ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመስራት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ መናገራቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
ከንቲባ ጎንግ ዜንግ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ማዕከል እንዲሁም ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ካለችው እና የአፍሪካ መግቢያ በር ከሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ጋር ተቀራርቦ መስራት የሁለቱን ከተሞች የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በቀጣይም የእህትማማች ግንኙነት በመመስረት በንግድ ፣ በቱሪዝም ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ፣ በአቅም ግንባታ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው መንገዶች ከሥምምነት ላይ ደርሰዋል::