ኢትዮጵያ ተጨማሪ ቅርሶችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት ላይ መሆኗ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጰያ ተጨማሪ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሠነድ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀች መሆኑን የኢትዮጰያ የቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር) ለብዙኃን መገናኛ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የመልካ ቁንጡሬ መካነ ቅርስን በፈረንጆቹ 2024 በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል የልየታና የሠነድ ዝግጅት ተጠናቆ ለሚመለከተው አካል መላኩን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የኢሳ ባሕላዊና አፋዊ የሕግ ሥርዓትን የሚዳሰስ ቅርስ ውስጥ ለማስመዝገብ እየተሞከረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢሳ ሥርዓት ከሦስት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር በመተባበር የጋራ ቅርስ እንዲሆን ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የጋራ ቅርሱ የምዝገባ ሂደት በኢትዮጵያ ፣ በሶማሊያና በጁቡቲ ትብብር የሚከናወን ሲሆን የሠነድ ዝግጅቱን ኢትዮጵያ በባለቤትነት እያከናወነች መሆኑንም አስረድተዋል።
ቀደም ሲል የደመራና የጥምቀት በዓል እንዲሁም የፊቼ ጨምበላላና የገዳ ባሕላዊ አስተዳደር በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገባቸው ይታወቃል።
ከኅዳር 24 እስከ ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በቦትስዋና ካሳኔ ከተማ በተካሔደው 18ኛው የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ጉባዔ ላይ የሐረሪ ብሔረሰብ የሹዋሊድ ክብረ በዓል በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሃብቶች የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ ዕድል እንደሚፈጥሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡