Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ሀገራት ዲፕሎማቶች በጋዛ ጦርነት እንዲያበቃ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀርመን፣ ፈረንሳይ እና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እስራዔል በጋዛ የምትወስደውን እርምጃ እንድታቆም ጠየቁ፡፡

ሚኒስትሮቹ እስራዔል በጋዛ የምትወስደውን ወታደራዊ እርምጃ እንድታቆም በጋራ በሰጡት መግለጫ ጠይቀዋል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና እስራዔል ጦርነቱን እንድታቆም የእርሳቸውን እና የአቻዎቻቸውን ሐሳብ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች “በፍጥነት እንዲታረቁ ፣ ታጋቾች እንዲለቀቁ ፣ በጋዛ ለሚሰቃዩ ንፁሐን ዜጎችም ተጨማሪ ሰብዓዊ ዕርዳታ በአስቸኳይ እንዲደርስ እና ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ላይ ተደርሶ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲበጅ መጠየቃቸውን አር ቲ ዘግቧል።

የብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን እና የጀርመኑ አቻቸው አናሌና ቤርቦክ፥ “በጣም በርካታ ንፁሐን ተገድለዋል” ብለው መፃፋቸውንም ነው የዜና ምንጩ ያመላከተው፡፡

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ÷ “የእስራዔል መንግሥት ዘመቻ የሃማስ መሪዎች እና አቀነባባሪዎች ላይ ብቻ ዒላማ ያደረገ ስለ መሆኑ እርግጠኛ መሆን እና የሚወሰደው እርምጃ አሸባሪዎችን ከንፁሐን የለየ መሆን አለበት” ብለዋል።

የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፥ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የቀረበውን “ሁለቱ ወገኖች ጠባቸውን እንዲያቆሙ” የሚጠይቅ ሐሳብ መደገፋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

በዛሬው ዕለት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን በእስራዔል በሚያደርጉት ጉብኝት በጋዛ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ ከግምት ውስጥ በማስገባት የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለሚወስዱት እርምጃ ግልፅ የሆነ ዓላማ እንዲኖራቸው እና ሥልት እንዲነድፉ ግፊት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.