እስራዔል ከሃማስ ጋር አዲስ ድርድር ልትጀምር መሆኑ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራዔል በሃማስ የተያዙ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በኳታር አማካኝነት አዲስ ድርድር ልትጀምር መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለመምከርም አንድ የእስዔል ከፍተኛ ባለስልጣን የኳታሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ቢን አብዱልራህማን ቢን ጃሲም አል ታኒን ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ትናንት ከሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በጋዛ የከፈቱትን ጦርነት ድል እስከሚያደርጉ ድረስ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በአቋማቸው ላይም ምንም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ነው ያስታወቁት፡፡
ጦርነቱ ሃማስ ትጥቅ ፈትቶ ጋዛ በእስራዔል የደኅንነት ቁጥጥር ሥር እስከምትውል ድረስ ይቀጥላል ማለታቸውን ኤዥያ ዋን ዘግቧል፡፡
የእስራዔል -ጋዛ ድብደባን ተከትሎ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚልቁ የጋዛ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
እንዲሁም እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት በእስራዔል -ሃማስ ጦርነት ምክንያት ከ20 ሺህ በላይ ንፁሐን ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተጠቅሷል፡፡