ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ማዚ ሜሌሳ በአሜሪካ ለማሟያ ምርጫ ቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አብዛኛውን መቀመጫ የያዘው የሪፐብሊካን ፓርቲ ኢትዮ -እስራዔላዊቷን ማዚ ሜሌሳ ፒሊፕ ለማሟያ ምርጫ ማቅረቡ ተገለጸ፡፡
ፓርቲው በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ በመልካም ሥማቸው የሚጠሩትን የሕግ አዋቂ ማዚ ሜሌሳ ፒሊፕ ለማሟያ ምርጫው እንዲወዳደሩ ያቀረበው ከፓርቲው የተባረሩትን ጆርጅ ሳንቶስ እንዲተኩ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ትውልደ-ኢትዮጵያዊቷ ማዚ ሜሌሳ አሁን ላይ በአሜሪካ የሕግ አዋቂ እና በትዳር ህይወታቸው የሰባት ልጆች እናት መሆናቸውን መረጃው ያመላክታል።
ማዚ ሜሌሳ ቀደም ሲል በእስራዔል መከላከያ ውስጥ በአየር ወለድ ምድብ ማገልገላቸውን ፎርዋርድ የተሠኘው የእስራዔል የዜና ምንጭ አስነብቧል፡፡
ማዚ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንጆቹ 2021 ላይ ለ“ፐብሊክ ኦፊስ” ተወዳድረው ለአራት ጊዜ መቀመጫውን ያገኘውን ዴሞክራት አስነስተዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2020 ላይ ዴሞክራቶች ባሸነፉበት የኒውዮርክ ፣ ሎንግ አይላንድ የምርጫ ወረዳ የ44 ዓመቷ ጠንካራ ሴት ተወዳድረው እንደሚያሸንፉና ሪፐብሊካኖች እንደሚተማመኑባት ተመላክቷል፡፡