ከበራሪ ምስክሮች መካከል
ጊዜ በሚዋጀው የታሪክ ዑደት ውስጥ ምንም ዓይነት ቀለም የማያጠፋውን የማይደበዝዝ አሻራቸውን ካኖሩ ጀግኖች መካከል ዛሬ አንዱን በምክንያት ላነሳው ወደድኩኝ፡፡
በራሪ! ደግሞም አስተማሪ! ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ምጥ ውስጥ በገቡበት ዘመን በሰማይ ቀዛፊ ሆነው ኢትዮጵያን ከጭንቅ የገላገሉ ገድል ሰሪ ባለ ታሪክም ጭምር፡፡
በስራቸው ብዙ ክንፎችን ያለመመለሙ ፤ የሀገርን ሰንደቅ ሊዳፈሩ ልባቸው የከጀለ የሰማይ በራሪዎችንም ያፈረሱና ስማቸው ከቀዳሚዎቹ መካከል የሚሰለፍ ነው፡፡
በዚያ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ አየር ሃይልን በሰማይ ይዘው የከነፉት ፤ ጠላትንም ብርክ ያስይዙት ከነበሩት በራሪ ምስክሮች መካከል አንዱ ከሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ሐይለሚካዔል ብሩ ጋር ወግ ተጋርተናል፡፡
ብርጋዴር ጄነራል ሐይለሚካዔል ብሩ ወቅቱን ሲያስታውሱ ሀገር ጦር ባወጁባት ጠላቶቿ ፊት ተሰብራ እንዳትታይ አጥንታቸውን ከከሰከሱላት እና ስጋቸውን ከቆረሱላት ተርታ ለመሰለፍ በኩራት የቆሙላት ውድ ልጇ እንደሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡
የጠላትን የጦር አውሮፕላኖች ከሚምዘገዘጉበት እንዴት ከጥቅም ውጭ እንዳደረጉ ተምዘግዛጊው ጀግና ሲያወጉም አንዳች ስሜት ውስጥን ይነዝራል፡፡
የኢትዮጵያ በራሪዎች በእብሪት ምስራቃዊ የሀገሪቱን ክፍል የወረረውን የጠላት ጦር ድባቅ በመምታት ለወገን የእግረኛ ጦር ወኔ ስለመሆናቸውም ታሪክ የማይዘነጋው ገድል ነው፡፡
አለፍ ብለን ስናነሳም ከአየር በአየር ውጊያ ባሻገር በጀግንነት ለቆሰሉት አስፈላጊ የህክምና እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶችን በማቅረብ ለሠራዊቱ አለንላችሁ ባይም ናቸው፡፡
ወቅቱን በጀግንነት የሚያስታውሱት ብርጋዴር ጄነራል ሐይለሚካዔል ብሩ ከድሬዳዋ በመነሳት ኢትዮጵያ እጅ እንድትሰጥ ለሻተው የጠላት ጦር ልጆቿ እንደንብ ተነስተው እንዳይሆኑ ማድረጋቸውን የዓመታት ድማር ባላፈዘዘው ወኔያቸው ሲናገሩ ደም ያሞቃሉ፡፡
ከሐርጌሳ በመነሳት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚፈነጩ የጠላት የጦር አውሮፕላኖችን ለመጣል በጥናት እና በብስለት የታጀበ ሥራ እንደተሰራም ይገልጻሉ፡፡
ጀግና ከራሱ አልፎ በማትደገም እስትንፋሱ ከሚዋደቅላቸው የሀገሩ ልጆች ቀድሞ ለመሰዋት አያወላውልምና ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት ንፁሃን የማይጎዱበትን ሰዓት በማመቻቸት ከፀሃይ መውጣት በፊት ይከንፋል፡፡
ማሸነፍ ግቡ ለእናት ሀገሩ መሞት ክብሩ ነውና የጠላትን መሳሪያዎች ዶግ ዓመድ በማድረግ ከአባቶቻቸው የወረሱትን ጀግንነት ክፉን በልቡ ላዘለው የጠላት ጦር እንዳይደገምህ ሲል በብርቱ ክንዱ ይገስጻል፡፡
ለዚህ ደግሞ አብሪ ምስክር የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ሐይለሚካዔል ብሩ መሪ ቀዛፊ አብራሪ ሆነው በሰማይ ላይ ያስመዘገቡትን ድል ልክ እንደ ትናንት ያስታውሱታል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ሲያስታውሱም ጀግንነቱ፣ የሀገር ዋልታ እና ማገርነቱን የብዙ ጀግኖችም መፍለቂያ ስለመሆኑም ተናግረው አያባሩም፡፡
የወቅቱ የኢትዮጵያውያን በራሪዎች ታሪክ አየር በአየር ውጊያ፣ በምድር የጠላትን ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና አቅርቦቶች ከጥቅም ውጭ ማድረግ መቻሉ በእብሪት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር የጣሰውን የጠላት ጦር ወደ ኋላ እንዲፈረጥጥ እንዳደረገውም ያስታውሳሉ፡፡
በራሪዎቹ በሰማይ ላይ በጀግንነት ሲከንፉ ለአፍታም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ በማይገባ የሀገር ፍቅር እና አትንኩኝ ባይ ወኔን እንደሀገራቸው የክብር ካባ ተላብሰው ነው፡፡
ሰብዓዊነት እንዲሁም ርህራሄም መገለጫቸው የሆነው የኢትዮጵያ አየር ሃይል አባላት ጀግኖች ዛሬም እንደ ትናንቱ የነበረውን ህብረት አጠናክረውና ለኢትዮጵያ ሰማይ መከታ ሆነው ስለመቀጠላቸውም ብርጋዴር ጀነራል ሐይለሚካዔል ብሩ አንስተዋል፡፡
ሰሎሞን ይታየው እንደፃፈው