ተመራማሪዎች በሰው አንጎል ህብረ-ሕዋስ የሚሰራ ኮምፒውተር ገነቡ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ሰው አእምሮ በጣም ከፍተኛ እና ውስብስብ የሆነ ምንም ዓይነት ነገር የለም በማለት ከሰው ሰራሽ ኮምፒውተር እንደሚልቅ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የሰው ልጅ የራስ ቅል ውስጥ የሚገኙ ህብረ-ህዋሳት መረጃን በብዛት እና በፍጥነት ማካሄድ የሚችሉት የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ሊስተካከለው ከሚችለው በላይ እንደሆነም ነው የሚነገረው፡፡
የሰው ልጅ ለብዙ ዓመታት የሰው አንጎልን የቀረበ ወይም የሚመስል ኮምፒውተርን ለመስራት ብዙ ሙከራዎች ተደርጓል፡፡
ሆኖም ይህ የሰው ልጅ አንጎል ህብረ-ህዋስን ተጠቅሞ ኮምፒውተር መገንባቱ ለእስካሁኑ ጥረት አንድ እርምጃ ያስኬደ ነው ሲሉ የዘርፉ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡
የሰው አንጎል ህብረ-ህዋስ እና ኤሌክትሮኒክስን ያጣመረው አዲሱ ኮምፒውተር ብሬንዌር ሲሉም መተግበሪያውን ሰይመውታል፡፡
ይሄን ቴክኖሎጂ የበለጠ በማስፋፋት ረገድ ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ እንደሆነም የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ኮምፒውተሩን ለገነቡት ለፌንግ ጉዖ (ኢ/ር) እና ቡድኑ አደራ ብለዋል፡፡
የሰው አንጎል በአማካይ ወደ 86 ቢሊየን የሚገመቱ የነርቭ ህዋሳት እና እስከ ኳድሪሊየን ሲናፕሶችን(የነርቭ ህዋሱ ወደሌላ የነርቭ ህዋስ እንዲተላለፍ የሚያግዝ) እንደሚይዝ ሣይንስ አለርት አስነብቧል።
እያንዳንዱ ነርቭ ደግሞ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሌሎች የነርቭ ህዋሳት ጋር የተገናኘ እንደሆነና ይህም እርስ በርስ ያለማቋረጥ እንዲገናኙ እንደሚያደርግም ነው የሚነገረው፡፡
በዚህም እውነተኛ የሰው ልጅ አንጎል ህብረ-ህዋስን በቤተ ሙከራ ውስጥ እንዲያድጉ በማድረግ ለብሬንዌር ኮምፒውተር እንደተጠቀሙትም ነው የተገለጸው፡፡
መደበኛ የኮምፒዩተር ሃርድዌር አውት ፑት እና ኢንፑት ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፥ ይህ ከሰው አንጎል ህብረ-ህዋስ የተሰራው ኮምፒውተር ግን ከዚህ በላቀ ዳታ በማንበብና ከዚያ አልፎም መረጃውን መሰረት በማድረግ እንደሚተነብይ ተገልጿል፡፡
በዚህም 240 የተቀዱ ድምጾች የተሰጡት ይህ ኮምፒውተር አንድ ድምጽን ለይቶ እንዲያወጣ ሲጠየቅ 75 በመቶውን ትክክለኛ ምላሽ መስጠቱም ነው የተነገረው፡፡