Fana: At a Speed of Life!

በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ መቻሉን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የሦስት ወራት አፈጻጸም በተካሄደበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት፥ በመንግስት የልማት ድርጅቶች በሆኑት በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በኢትዮ-ቴሌኮም እና በመሳሰሉ የመንግስት የልማት ተቋማት በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ ተችሏል፡፡

የገቢ አሰባሰቡን ለማሳደግም ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆን በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡

በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራዊ በሚደረገበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ከልማት አጋሮች ጋር በቅንጅት በመሰራቱ የውጭ ሃብት ግኝት ከማሳደግ ባሻገር የበጀት ጉድለትን መሽፈን ችለናልም ነው ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ፡፡

ታክስ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የፋይናንስ አስተዳደሩን ማጠናከር እና ማዘመን እንደሚገባ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሩብ ዓመቱ በጥቅል የሀገር ምርት፣ በነፍስ ወከፍ ገቢ፣ በገቢ ረገድና ሌሎችም የኢኮኖሚ መሻሻል አመላካቾች ዕድገት መታየቱም በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡

የሩብ ዓመቱ የመንግስት ወጪ 123 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ያጋጠመ የ34 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የበጀት ጉድለት በሀገር ውስጥ ምንጮች መሸፈኑ ተጠቅሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.