Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት ሚኒስቴር ከጣሊያን አቻው ጋር የትብብር መግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር እና የጣሊያን ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርትና ስልጠና መስክ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የትብብር መግባቢያ ሥምምነት ሠነድ ተፈራርመዋል፡፡

ሥምምነቱን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና የጣሊያኑ አቻቸው ጁሴፔ ቫልዳይታራ ተፈራርመውታል፡፡

ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም በተለይም ለሁሉም ዜጋ ያለምንም የኢኮኖሚ ደረጃ ልዩነት ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለማቅረብ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አንስተዋል፡፡

ጁሴፔ ቫልዳይታራ በበኩላቸው ጣሊያን በቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና፣ በቋንቋና ባህል እንዲሁም በተማሪዎችና መምህራን ልውውጥ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡

የተፈረመው የትብብር ሥምምነት ሠነድ በሀገራቱ መካከል የሚደረገውን የትምህርትና ስልጠና ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት መካከል ስትራቴጂክ የሆነ የትምህርትና ሥልጠና ትብብር እንዲኖር ያስችላል ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.