Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈፅሙ በተገኙ 86 የስፖርት ውርርድ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድን ሽፋን በማድረግ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈፅሙ በተገኙ 86 የስፖርት ውርርድ ( ቤቲንግ) ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡

የስፖርት ውርርድ ቤቶችን ጨምሮ ጫት መቃሚያና ሺሻ ማጨሻ ቤቶች የወንጀል ፈፃሚዎች መሰባሰቢያና የወንጀል ድርጊት መጠንሰሻ በመሆን በህብረተሰቡ ላይ ስጋት እየፈጠሩ እንደሚገኙ ሲገለፅ መቆየቱን ፖሊስ አስታውሷል፡፡

በዚህም የአዲስ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከህብረተሰቡ ጥቆማ በመነሳት ባደረገው ጥናት አዋኪ ድርጊት በሚፈፀምባቸው ቤቶች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በፖሊስ መምሪያው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዲቪዚዮን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጳውሎስ ደምሴ እንዳሉት÷ እርምጃ የተወሰደባቸው የስፖርት ውርርድ ቤቶች ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ከወሰዱበት ክፍለ ከተማ ውጪ በመስራትና ያለ ንግድ ፈቃድ በዘርፉ ተሰማርተው የተገኙ ናቸው።

ሕጋዊነትን ሽፋን በማድረግ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን ዓላማ የሚያስቱ ሕገ ወጥ ተግባራትና ለፀጥታ ስጋት የሚሆኑ ሌሎች አዋኪ ድርጊቶች በሚፈፀሙባቸው ቤቶች ላይ የተጀመረው እርምጃ እንደሚቀጥል መጠቆማቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ህብረተሰቡ የአካባቢው ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋገጥ መረጃና ጥቆማ የመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.