የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆናቸውን የጃፓን ባለሀብቶች ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆናቸውን በኢትዮ-ጃፓን የኢንቨስትመንት ፎረም የተሳተፉ የጃፓን ባለሀብቶች ገለፁ፡፡
በፎረሙ የተሳተፉ የጃፓን ባለሀብቶች እና የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የቦሌ ለሚና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎብኝተዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በጉብኝታቸው የፓርኮቹን መሰረተ ልማት፣ ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ እንዲሁም የባለሀብቶችን ተሳትፎ ተመልክተዋል፡፡
በፓርኮቹ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ስለሚያገኟቸው የኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎችና ማበረታቻዎች ዙሪያም ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
በኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ዘመን ጁነዲን፥ በኢትዮጵያ እና በጃፓን መካከል የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ቢኖርም በኮርፖሬሽኑ ስር በሚተዳደሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የጃፓን ባለሀብቶች ያላቸው ተሳትፎ እንደ ግንኙነቱ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ይህንን ለመቀየርና ባለሀብቶቹን ለማስተናገድ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል።
የጃፓን ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተለይም በማምረቻው ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውንና በቀጣይም በፓርኮች ያለውን የጃፓን ባለሀብቶች ተሳትፎ ለማሳደግ ኮርፖሬሽኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በጃፓን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የጃፓን ባለሀብቶች የልዑካን ቡድንን የመሩት የኢንስፓየር አፍሪካ ማህበር ዳይሬክተር ያማጉቺ÷ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በማምረቻው ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በመሰረተ ልማት የተሟሉና ምቹ የስራ ከባቢ ውስጥ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
የጃፓን ባለሀብቶች በፓርኮቹ እንዲሰማሩ ባለሀብቶቹን የመለየት ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡