Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ልማት የጎረቤት ሀገራትን አብሮ ማደግ ማዕከል ያደረገ ነው – ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር )

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት የአካባቢውን ሀገራት የልማትና የለውጥ ፍላጎት ማዕከል ያደረገ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሯ ከሲ ጂ ቲ ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እያደገ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የባሕር በርን የተመለከተው ሥጋት ግልጽና አሁናዊ ሆኗል፡፡

ይህም የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረጉ ውይይቶችና የሰጥቶ መቀበል ስምምነቶችን ማዕከል ያደረገ እንደሆነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት 10 ዓመታት የአፍሪካ ሀገራትን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በርካታ ሥራዎችን ስትሠራ ቆይታለች ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የመሰረተ ልማት ትስስርን በእጅጉ የሚፈልግ መሆኑ ገልጸው÷ ይህንን በማሳካት ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያም የድርሻዋን በማበርከት የጥቅሙ ተካፋይ ለመሆን እየሠራች መሆኗ አረጋግጠዋል፡፡

ሌሎቹን በማራቅና ወደ ሌሎቹ በመቅረብ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሳይሆን ከኢትዮጵያ የለውጥና የልማት ፍላጎት አንጻር በማየት ብቻ ነው ወደ ብሪክስ አባልነት የተገባው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓየር ንብርት ለውጥ እያስከተለ ያለውን የአደጋ ተጋላጭነት ለመከላከል ባደረገችው ጥረትም ላለፉት አምስት ዓመታት 32 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች መትከሏን አስገንዝበዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብትን የመንከባከብና አካባቢን አረንጓዴ የማልበስ ሀገራዊ ሥራዋም በዓለም ቀዳሚ ሀገር ያደርጋታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ እስካሁን የምታገኘው የታዳሽ ኃይል ሽፋን ከ45 በመቶ ብዙም ያልተሻገረ ሲሆን÷ የሃገሪቱን የሃይል ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ የሆነው የታዳሽ ሃይል አማራጮችን ማስፋት ነው ሲሉም አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.