Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም በኦሮሚያ ክልል አገልግሎቱን ለማዘመን የሚያስችል ሥምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዲሁም ከሸገር ከተማ አሥተዳደር ጋር አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የፈረሙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መስከረም ደበበ እንዲሁም የሸገር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ሥምምነቱ÷ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የዞኖች፣ የወረዳና የቀበሌ አስተዳደር ቢሮ ሥራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና በዲጅታል አሰራር የታገዙ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን እንዲሁም የተገልጋዮችን የአገልግሎት እርካታ ለመጨመር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም በሸገር ከተማ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ዉጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻልና በከተማዉ ያለዉን የዲጂታል አገልግሎቶች ትግበራ ዓለም አቀፍ ደረጃና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ ሥምምነት ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም የተለያዩ ቢሮዎችን እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በቀላሉ ለማስተሳሰር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት ሥርዓቱን በማዘመንም አስተማማኝ፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መስከረም ደበበ ገልጸዋል።

የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ( ዶ/ር) በበኩላቸው የዉል ሥምምነት መፈረሙ የከተማዋን የስማርት ሲቲ ፕሮግራም ዕዉን ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።

በምንተስኖት ሙሉጌታ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.