Fana: At a Speed of Life!

አፕል አዳዲስ አይፓድና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን ለገበያ ሊያቀርብ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፕል ኩባንያ አዲስ ሞዴል የሆኑትን የአይፓድ እና ኮምፒውተር ምርቶችን ገበያ ላይ ለማዋል ዝግጅት መጨረሱን አስታውቋል፡፡

ምርቶቹ ኩባንያው ያጋጠመውን የሽያጭ መቀዛቀዝ ያሻሽላሉ የተባለ ሲሆን በመጨው መጋቢት ወር ገበያ ላይ እንደሚውሉ ተጠቁሟል፡፡

በአዳዲስ ምርቶቹ ውስጥ ቀደም ሲል ገበያ ላይ የነበሩት አይፓድ ኤር፣ አይፓድ ፕሮ እንዲሁም የማክቡክ ኤር ላፕቶፖች በአዲስ ሞዴል ይዘምናሉ የተባሉ ሲሆን አዲሱ የመለያ ስማቸው በይፋ አልተገለፅም፡፡

አዳዲሶቹ የአይፓድ ኤር ሞዴሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት አይነት መጠን ይቀርባሉ የተባለ ሲሆን የማክ ቡክ ኤር ላፕቶፖች ደግሞ ፈጣን በተባለው ኤም3 ማቀነባበሪያ (ፕሮሰሰር ዩኒት) ዘምነው ለገበያ እንደሚቀርቡ ተመላክቷል፡፡

አፕል ኩባንያን የ15 በመቶ ገቢ ይሸፍናሉ የተባሉት የማክኤር ላፕቶፖች እና አይፓዶች በሸማቾች የግዥ ፍላጎት መቀነስ ምክንያት የገበያ መቀዛቀዝ አጋጥሟቸው እንደነበር ብሉምበርግ አስነብቧል፡፡

የምርቶቹ ገበያ የቀነሰው በአዳዲስ ሞዴሎች ባለመዘመናቸው ምክንያት መሆኑ ተገለፀ ሲሆን፤ የአፕል ኩባንያ በፈረንጆቹ 2023 በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አይፓዶችን እና ማክ ኤር ላፕቶፖችን በአዳዲስ ሞዴሎች ሳይተካ ቀርቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.