Fana: At a Speed of Life!

7ኛው ዙር የኦዳ አዋርድ ታኅሣሥ 11 ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮ ኦዳ አዋርድ ለ7ኛ ጊዜ ታኅሣሥ 11 ቀን እንደሚካሄድ አስተባባሪዎቹ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የኦዳ አዋርድ በዚህኛው ዙር ከሀገር አልፎ አፍሪካውያን የሚሸለሙበት መድረክ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን የነፃነት አርማ መሆኗን ያስታወሱት አስተባባሪዎቹ፤ ይህንን በኪነ-ጥበቡ ዘርፍም መድገም እንደሚገባ አመልክተዋል።

በመሆኑም በዘንድሮ ኦዳ አዋርድ ከሀገር ውስጥ ጥበበኞች ባሻገር ከ7 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተመረጡ ባለሞያዎች እውቅና ያገኛሉ ተብሏል።

በ7ኛው ዙር ለሽልማት የሚበቁ እጩ ስራዎች በ2015 ዓ.ም ከመስከረም 1 እስከ ጳጉሜን 6 የተሰሩ ብቻ ይሆናሉ ተብሏል።

የአመቱ ምርጥ አልበም፣ የአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ የአመቱ ምርጥ ቪዲዮ ክሊፕ፣ የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ስቱዲዮ፣ የአመቱ ምርጥ ሴት ድምፃዊ፣ የአመቱ ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፣ የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ጥምረት፣ የአመቱ ምርጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስት እንዲሁም የአመቱ ምርጥ ዘመናዊ ሙዚቃዎች ተለይተው ለሽልማት እንደሚበቁ ተነግሯል።

ኦዳ አዋርድ በኢትዮጵያ በሁሉም ቋንቋዎች የሚሰሩ የኪነጥበብ ስራዎች እኩል እድል አግኝተው እንዲበረታቱና ለኢትዮጰያ የኪነ ጥበብ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የሚዘጋጅ መሆኑም በአስተባባሪዎች ተገልጿል፡፡

በሽልማት ስነ-ስርዓቱ የመፅሐፍ እና የህይወት ዘመን ተሻለሚዎችም ይኖራሉ ነው የተባለው።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.