Fana: At a Speed of Life!

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለማስተዋወቅ ያለመ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የበለጠ ለማስተዋወቅ ያለመ መርሐ ግብር በባሌ ሮቤ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊና የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራን ጨምሮ ሌሎች የፈዴራልና የክልሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ታድመዋል።

በመርሐ ግብሩ ፓርኩን በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጉልህ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት ዕውቅና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም በመርሐ ግብሩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ያሉበትን ችግሮች በመፍታት የመስህብነት አቅሙን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ታዳሚዎቹ ከዕውቅና መርሐ ግብሩ በኋላ በፓርኩ የተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት በማድረግ ፓርኩ ያለበትን ሁኔታ እንደሚመለከቱ ኢዜአ ዘግቧል።

ፓርኩ ዋቢ ሸበሌ፣ ዱማል፣ ያዶትና ወልመል የተሰኙ ወንዞች የሚፈሱበትና ቀይ ቀበሮ፣ የደጋ አጋዘንና ሌሎችም ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ አዕዋፋትና ዕጽዋት መገኛ መሆኑ ይታወቃል።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) 45ኛው ጉባኤ ላይ በቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.