Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ለናይጄሪያ ሰብዓዊ ድጋፍ ልታደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ለናይጄሪያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ማዕከል ልታቋቁም መሆኑ ተገለጸ፡፡

ማዕከላቱ በሀገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች በአደጋ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እንደሚያገለግሉ ናይራሜትሪክስ አስነብቧል፡፡

የናይጄሪያ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና ድሕነት ቅነሳ ሚኒስትር ዶ/ር ቤታ ኤዱ፥ ሀገራቱ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ማዕከላትን ለማቋቋም ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

ናይጄሪያ በሰሜን – ምሥራቅ በኩል ሰርጎ-ገቦች በሚፈጥሩት የሽብር ተግባር ሰብዓዊ ቀውስ እንደደረሰባት ተገልጿል፡፡

በሌሎች የሀገሪቷ ክፍሎችም ከተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ናይጄሪያ ሥር ለሰደደ ድሕነት መዳረጓ ነው የተጠቆመው፡፡

ዶ/ር ቤታ ኤዱ በዱባይ ከነበራቸው የኮፕ 28 ቆይታ ጎን ለጎን በጉዳዩ ላይ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ፣ ከዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ፣ ከኢስላማዊ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት እንዲሁም ከቀይ ጨረቃ ማኅበር አካላት ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከውይይቱ በኋላም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ናይጄሪያ መጥተው ሁኔታውን ለመመልከት እና ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚቻልበትን ሥርዓት እንደሚያበጁ ቃል መግባታቸውን አመላክተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.