በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት ከተከላከልን የምናልማትን ዓለም እንኖርባታለን – ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት የምንከላከል ከሆነ የምናልማትን ዓለም እንኖርባታለን ሲሉ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የሀገራት መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የግሉ ዘርፍ፣ ሲቪል ማኅበራት፣ ምሁራን ወጣቶችና ሴቶች የተሳተፉበት በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት ለማስቆም በሚመክር ጉባዔ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ÷ መድረኩን የተለየ የሚያደርገው ፆታ ላይ መሠረት ያደረገ ጥቃት ሲደርስ እኛ ወንዶችና ወጣቶች በመከላከሉ ረገድ የግንባር ቀደምነቱን ሚና መውሰድ እንዳለብን ስለምናውቅ ነው ብለዋል፡፡
ሴቶች እና ሕፃናት እውነተኛ ነፃነትና እኩልነት ከመብታቸው ጋር ተከብሮላቸው የሚኖሩባት ዓለም እንዲፈጠር የሁሉም አፍሪካዊ ፍላጎት እንደሆነ ተናግረዋል።
በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት የምንከላከል ከሆነ የምናልማትን ዓለም እንኖርባታለንም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ በበኩላቸው የወንዶች ሚና ላይ ትኩረት አድርጎ በሚወያየው መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢኮኖሚ ከፆታዊ ጥቃት ተጋላጭነት ጋር ትሥሥር እንዳለው አንስተዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ ኅብረትን የሴቶች እና ወጣቶች የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ጉዳይ በኢኒሼቲቭን ደረጃ መጀመሩን ተናግረዋል።
ኢኒሼቲቩ የአፍሪካ ሴቶች እና ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ትሥሥር በመፍጠር ገንዘብ አግኝተው ማምረት እና አገልግሎት መሥጠት የሚችሉበትን መንገድ እንደሚያመቻችም ጠቁመዋል።