የግሉ ዘርፍ ለኢትዮጵያ የዕድገት ሞተር ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ዕድገት የግሉ ዘርፍ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት ለማሳደግና ድሕነትን ለመቀልበስ ባለን አቅም ሁሉ ሠርተናል ብለዋል።
በርካታ ተግዳሮቶችን እየተቋቋምን ዕድሎቻችን ላይ አተኩረን ማሻሻያዎችን በመተግበር ውጤት ማስመዝገብ ጀምረናልም ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ራዕያችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያሏትን ዕምቅ አቅሞች መለየትና ባሏት ተቋማት እንዲሁም በሠለጠነ የሰው ኃይሏ ዕድገቷን ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ ዘርፈ ብዙ የዕድገት ጎዳናን የተከተለ ነው በማለት ገልጸው፤ ይህም ፍትኀዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ እንደሚረዳ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ቅድሚያ ሠጥታ እየሠራች እንደሆነና በተለይም የማዕድኑ ዘርፍ ለዕድገቷ ተሥፋ ሠጪ ውጤት የሚታይበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከድሕነት የምትላቀቀው በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ አማራጮችን በመፍጠር እንደሆነ ታምኖበት በሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህም መሠረት እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን እና ባንክ ያሉት ቁልፍ የሀገሪቷ የምጣኔ ሐብት ዘርፎች ከመንግስት መር ወደ ግሉ የማሸጋገር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ይህ ሀገር በቀል የፖሊሲ ማሻሻያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያድግና የውጭ ባለሐብቶችም በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚያበረታታ አንስተዋል፡፡
የሀገሪቷን ምጣኔ ሐብት ለማሳደግ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለሁሉም ክፍት አድርገናል ብለዋል።
ግብርና፣ ቱሪዝም፣ አይሲቲ እና የመሣሠሉትም የሀገሪቷ የዕድገት ምሦሶዎች እንደሆኑ ገልጸው፤ ዘርፉን ለማዘመንና ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ የግብርናው ዘርፍ ቀድሞ ከነበረበት ተላቆ ከፍተኛ ምርት መሰብሰብ ወደሚቻልበት ደረጃ መሸጋገር እንደቻለም ለአብነት አንስተዋል፡፡
እንደ ስንዴ፣ ቡና እና አቮካዶ ያሉ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶች ላይም በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ባለፉት አምስት የዕድገት ዓመታት አጠቃላይ መታረስ የሚችለውን መሬት ከ15 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር ወደ 22 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር ማሳደግ መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡