Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ቀን ዛሬ በመላው አህጉሪቱ ታስቦ ዋለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በየዓመቱ በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 25 የሚከበረው የአፍሪካ ቀን ዛሬም በመላው አህጉሪቱ ታስቦ ውሏል።

ከዚህ ቀደብ በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር የቆየው እለቱ ዛሬ በቪዲዮ በሚካሄድ ኮንፈረንስ ታስቦ መዋሉን ህብረቱ አመላክቷል።

ይህም የቪዲዮ ኮንፈረንስ “የመሳሪያን ድምፅ ማጥፋት” ሚለውን የዘንድሮው የህብረቱ መሪ ቃል ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር አስተሳስሮ እንደተወያየበት ነው ያመለከተው።

ህብረቱ ቀኑን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በኮቪድ-19 ምክንያት ሁነቶችን ማስተናገድ ባለመቻሉ በሚደረጉ የቪዲዮ ኮንፈረንሶች ላይ የዘንድሮውን መሪ ቃል በዚህ የወረርሽኝ ወቅት እንዴት ማሳካት ይቻላል በሚለው ላይ መክሯል።

ከዛሬው በተጨማሪ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሌሎች ሁለት ኮንፈረንሶች እንደሚካሄዱ አመልክቷል።

ዕለቱን በማስመልከት መልዕከት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “በብዙ ጸጋ የታደለችው፣ ሁሉም ዓይነት ብዝኃነት የሞላባት አህጉራችን መድረሻዋ መልከ ብዙ ብልጽግና ነው” ብለዋል።

“ዛሬ የአፍሪካ ቀንን ስናከብር የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ፣ አንድነታችንን እናጠንክር” ሲሉም በመልዕክታቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ቀን በፈረንጆቹ ግንቦት 25 ቀን 1963 የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ የተመሰረተበትን ቀን ለማስታወስ የሚከበር ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.