Fana: At a Speed of Life!

በ3 ወራት ከ72 ሚሊየን ዶላር በላይ ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መገኘቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 38 ነጥብ 7 ሺህ ቶን ምርት ወደ ውጭ በመላክ ከአምራች ኢንዱስትሪው ከ72 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ÷ በሩብ ዓመቱ የኢንዱስትሪው ዘርፍ አበረታች ውጤት ሊያስመዘግብ የቻለው ግብዓቶችን በማቅረብ፣ ገቢ ምርቶችን በመተካትና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ነው ብለዋል።

ለጨርቃጨርቅ፣ ለምግብና መጠጥ፣ ለኢንጂነሪንግ እንዲሁም ለኬሚካልና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ከ2 ሚሊየን ቶን በላይ የተለያዩ ግብዓቶች ማቅረብ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ተኪ ምርት መጠን ለማሳደግ በተደረገው ድጋፍና ክትትል 366 ሚሊየን ዶላር ማዳን መቻሉንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

በሩብ ዓመቱ አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ በኩል የዕቅዱን 86 ነጥብ 8 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የገበያ ትሥሥር የተፈጠረላቸው ኢንዱስትሪዎች ቁጥርም ጨምሯል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ÷ የመሬት፣ የመሥሪያ ቦታ፣ የፋይናንስና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማሻሻል የአምራች ኢንዱስትሪውን አፈፃፀም ማሳደግ መቻሉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሚኒስትሮች የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሀገር ውስጥ ምርቶች በመንግሥት ግዥ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው አቅጣጫ መቀመጡም ተነግሯል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.