የእስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁም ሥምምነት ተግባራዊ መደረግ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤልና ሃማስ ለአራት ቀናት የተኩስ አቁም ለማድረግ የደረሱት ሥምምነት በዛሬው ዕለት ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ተሰምቷል፡፡
በጦርነት ውስጥ የሚገኙት እስራኤል እና ሃማስ ከቀናት በፊት ለአራት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ሥምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጅ በተፋላሚ ሃይሎች የተደረሰው የተኩስ አቁም ሥምምነት በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይደረግ መቆየቱን ቲ አር ቲ ዘግቧል፡፡
በዛሬው ዕለትም በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 7 ሰዓት ላይ የተኩስ አቁም ሥምምነቱ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ነው የተገለጸው፡፡
በሥምምነቱ መሰረትም ሃማስ እስካሁን አግቶ የያዛቸውን 50 እስራኤላውያን የሚለቅ ሲሆን÷ እስራኤል በበኩሏ በሀገሪቱ የታሰሩ150 ፍልስጤማውያንን የምትፈታ ይሆናል፡፡
ከዚህ ባለፈም በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰብዓዊ እርዳታ፣ ነዳጅ እና መድሃኒቶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
እስራኤልም በጋዛ ሰርጥ ሁሉም አካባቢዎች ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደምታቆምም ተገልጿል፡፡
49ኛ ቀኑን ባስቆጠረው የእስራኤል እና ሃማሰ ጦርነት እስካሁን በጋዛ ከ14 ሺህ በላይ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡