38 ጥርስ ያላት ህንዳዊት በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ተመዘገበች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ26 ዓመቷ ህንዳዊት ከሌሎች በተለየ 38 ጥርሶች ያሏት በመሆኑ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለመስፈር በቅታለች።
ካልፓና ባላን የተባለችው ህንዳዊቷ ብዙዎች በተፈጥሮ ካላቸው አማካይ የጥርስ ብዛት ስድስት ተጨማሪ ጥርሶች እንዳሏት ታውቋል፡፡
ይህም የሰው ልጅ ሊኖረው ከሚችለው በላይ ‘ብዙ ጥርስ ያሏት’ በሚል በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ለመመዝገብ እንዳበቃት ጊነስ ወርልድ ሪከርድስ አስታውቋል።
ባላን የሰው ልጅ ሊኖረው ከሚገባው በላይ በታችኛው መንጋጋ አራት በላይኛው መንጋጋ ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ጥርሶች አሏት።
ተጨማሪ ጥርሶቿ ማደግ የጀመሩት ገና ታዳጊ በነበረችበት ጊዜ እንደነበር እና መጀመሪያ ላይ ልታስነቅል ፈልጋ የጥርስ ሀኪሞች እድገታቸውን እስኪጨርሱ መጠበቅ እንዳለባት ነግረዋት እንደቆየች ገልፃለች።
በኋላም ጥርሶቹ ምንም ዓይነት ህመም የማያስከትሉ ከሆነ ላለማስወገድ እንደወሰነች ተናግራለች፡፡
ገና ያልወጡ ሁለት ተጨማሪ ጥርሶች ያሏት በመሆኑም ወደፊት ክብረ ወሰን ልታሻሽል እንደምትችል የጥርስ ሐኪሞቿ እንደነገሯት መግለጿን ዩ ፒ አይ ዘግቧል።