Fana: At a Speed of Life!

ጽንፍ የወጡ ትርክቶች ሁሉንም በሚያግባቡ ትርክቶች ሊተኩ ይገባል – አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጽንፍ የወጡ ትርክቶች ሁሉንም በሚያግባቡ ትርክቶች ሊተኩ እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እንዲሁም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አፈ ጉባኤዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፥ በሀገራችን በስፋት የሚንጸባረቁ የመነጠልና የጠቅላይነት አስተሳሰብን የያዙ ሁለት ነጠላ ትርክቶች ሁሉንም በሚያግባቡ የጋራ ትርክቶች መተካት አለባቸው ፡፡

ጽንፍ የወጡ አካሄዶችን በመታገልና በማረም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን መቻቻልንና ሁሉንም ሃይማኖቶችና ባህሎች የሚያስተናግድ የጋራ ትርክት ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ለትርክቶች መነሻ የሆነውን ታሪክም እንደመማሪያ ቆጥሮ ትርክቱን እያረሙ የማለፍ እድል የዚህ ትውልድ ሃላፊነት መሆኑን በመጥቀስም፥ አሁን ያለው ስርዓት ከጠቅላይነትም ከተነጣይነት አመለካከት የወጣ ኢትዮጵያ የብዙ ማንነቶች ፣ብሄር ብሄረሰቦች፣ ቋንቋዎችና ባህሎች ሀገር መሆኗን የተቀበለና ያከበረ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት የሚከበርባት ሀገር መሆኗን በመገንዘብ አንድነትን አጉልቶ የሚያሳይ ስራ በመሰራት ላይ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡

የደቡብ ምዕራብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወንድሙ ኩርታ በበኩላቸው፥ በሀገራችን አብሮ ከመኖርና ከማደግ ይልቅ መለያየትን፣ ጥላቻን እና ጽንፈኝነትን የሚሰብኩ ትርክቶች ይንጸባረቁ እንደነበር አስታውሰዋል።

በቀጣይ የጋራ በሚያደርጉንና ወደፊት በሚራምዱን ጉዳዮች ላይ ብቻ ልናተኩር ይገባልም ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር በርካታ የጋራ ከሚያደርጉን የጋራ ታሪኮች አሉን ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አፈ ጉባኤ አዳማ ባዬ ናቸው፡፡

ለሀገራችን ነጻነት በጋራ የከፈልነው ዋጋና ለህዳሴው ግድብ ልማት ያደረግነው የጋራ አስተዋጽኦንም አቶ አዳማ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በፈትያ አብደላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.