የዓለማችን ሙቀት በ 2 ዲግሪ ሴሊሺየስ መጨመሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ዓለማችን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የ 2 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሙቀት መጠን ጭማሬ ማስመዝገቧ ተገለጸ፡፡
የኮፐርኒከስ ምክትል ዳይሬክተር ሳማንታ በርጅስ እንዳሉት ÷ ባሳለፍነው ዓርብ የተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን የኢንዱስትሪው አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት (ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ በፊት) ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛው ነው፡፡
ዓለማችን በዚሁ ከቀጠለች የሙቀት መጠኗ ከ2 ነጥብ 5 እስከ 2 ነጥብ 9 ዲግሪ ሴሊሺየስ ጭማሬ እያሳየ መሄዱ አይቀርምም ነው የተባለው፡፡
በተመሳሳይ የዓለማችን የዓየር ብክለት መጠንም ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መሄዱ ተመልክቷል፡፡
የዓለማችንን የዓየር ብክለት መጠን በ1 ነጥብ 2 በመቶ እንዲጨምር ያደረጉት ምክንያቶች ከተሽከርካሪዎች የሚወገደው የተቃጠለ ዓየር ፣ የተቃጠለ ዘይት እና ጋዝ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደሚያመላክተው አባል ሀገራቱ በ2015 የገቡት የፓሪስ የዓየር ንብረት ሥምምነት በአሥርት ዓመታት የዓለምን ሙቀት በ 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴሊሺየስ ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡
በሥምምነቱ የዓየር ብክለት መጠናቸውንም በ42 በመቶ ለመቀነስ ቃል ገብተው ነበር፡፡