አቶ ጥላሁን ከበደ ከወላይታ ሶዶና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ ከወላይታ ሶዶ ከተማ እና አካባቢው ማህበረሰብ ጋር እየተወያዩ ነው፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ልዩ የሆነ ከተማ አቀፍ እና ክልላዊ የሰላም የፍቅር እና የመቻቻል ተምሳሌት ክልል መስርተን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብተናል፡፡
አቶ ጥላሁን ክልሉ ተመስርቶ ስራ ጀምረናል፤ በይፋ ታሪካዊ የማብሰሪያ ቀኑን በጋራ እናበስራለን ሲሉም ተናግረዋል።
ይበልጥ መቀራረብ እና አብሮ በመስራት ከምስረታው ማግስት ጀምሮ ሕዝቡን የለውጥ ማዕከል በማድረግ ብልፅግናችንን እያረጋገጥን ነው ብለዋል ርዕሰ መስተደድሩ፡፡
የወላይታ ዞን አስተዳደሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በበኩላቸው÷ በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አብሮ የመበልፀግ እድል የተፈጠረበት ምዕራፍ መሆኑን ገልፀዋል።
ለይፋዊ የክልል ምስረታ ማብሰሪያ ፕሮግራም ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ እንግዶች እየተጠበቁ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ለክልሉ ምስረታ የማብሰሪያ ፕሮግራም የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ይፋዊ የማብሰያ ፕርግራም የፊታችን ሐሙስ እንደሚካሄድ የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡