የኢትዮጵያ እና ኩባ ግንኙነት በደም የተሳሰረ ነው – የኩባ ምክትል ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኩባው ምክትል ፕሬዚዳንት ሳልቫዶር አንቶኒዮ ቫልዴዝ ዛሬ በኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
የአበባ ጉንጉን ባስቀመጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግርም÷ የኢትዮጵያ እና ኩባ ግንኙነት ታሪካዊ እና በደም የተሳሰረ ነው ብለዋል፡፡
ግንኙነቱ በይፋ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየጊዜው በተለያዩ መስኮች እየጎለበተ መምጣቱንም አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ እና በኩባ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን በሥነ- ሥርዓቱ ላይ መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ትናንት ምሽት አዲስ አበባ የገቡት የኩባ ምክትል ፕሬዚዳንት÷ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዙ ውይይቶችን ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡