ሠዓሊ ጁሊ ምሕረቱ የአፍሪካን ኪነ-ጥበብ የዓለም ክብረ-ወሰን ዳግም ሰበረች
አዲስ አበባ፣ ኅዳር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መኖሪያዋን በአሜሪካ ያደረገችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሠዓሊ ጁሊ ምሕረቱ የአፍሪካን ኪነ-ጥበብ የዓለም ክብረ-ወሰን በድጋሚ ሰበረች።
ጁሊ ምሕረቱ ክብረ-ወሰኑን የሰበረችው “ወከርስ ዊዝ ዘ ዳውን ኤንድ ሞርኒንግ” የተሠኘ ረቂቅ ሥዕሏን በኒውዮርክ ዖርሊያንስ በተዘጋጀ የሥዕል ዐውደ-ርዕይ ላይ በ10 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር በመሸጧ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ዓውደ-ርዕዩ የተዘጋጀው በፈረንጆቹ 2005 ላይ ተጽዕኖ ያሳረፈውን የካትሪና አውሎ ንፋስ ለማሰብ እና ምላሽ ለመሥጠት ነው፡፡
10 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር የተቆረጠለት ይህ ረቂቅ ሥዕል ያሸነፈው በተፎካካሪዎች የሚቀርበው ዋጋ ቀስ በቀስ እያደገ ሄዶ በመጨረሻ ከ9 ነጥብ 5 ሚሊየን 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ላይ ደርሶ ነው ተብሏል፡፡
ይህ ድንቅ ነው የተባለለት የጁሊ ምሕረቱ ከቀለም እና አክሪሊክ የተሠራ ረቂቅ ሥዕል ሥያሜውን ያገኘው በ1920ዎቹ ከተፃፈው ላንግስተን ሂዩጅስ የግጥም ሥራ ነው ተብሏል፡፡
የ52 ዓመቷ ጁሊ ምሕረቱ÷ በፈረንጆቹ 1977 ከቤተሰቦቿ ጋር አሜሪካ መኖር ከጀመረች በኋላ ሥሟ በአፍሪካ ኮንቴምፖራሪ የሥነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ በፍጥነት እያደገ መምጣቱንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የጁሊ ምሕረቱ የሥነ-ጥበብ ሥራ ÷ ባለፈው ወር 9 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር በመሸጥ ክብረ-ወሰን ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡
ጁሊ ምሕረቱ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቀጣዩን የቢኤምደብሊው የተመረጠ መኪና በሥዕል ሥራዋ እንድታስውብ መመረጧ ይታወቃል።